የአርባምንጭ ከተማ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረኃይል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩና ሲነገዱ የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊና ም/ከንቲባ አቶ ምህረቱ ተሰማ ገልጸዋል።
በአርባምንጭ ከተማ ባለፉት ወራቶች በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኙ የነዳጅ ምርቶች፣ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተያዙ የተለያዩ ዓይነት ዕቃዎች አልባሳትን ጨምሮ የህገወጥ የመንገድ ዳር ንግድ ሲያካሂዱ የተወረሱ በተለያየ አይነት ያላቸው አጠቃላይ ቁጥራቸው ወደ 1,773 የሚደርሱ የተለያየዩ ዕቃዎችን ግብረኃይሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኃላፊው ተናግረው አጠቃላይ ንብረቶች በገንዘብ ሲተመን ከ150 ሺህ ብር በላይ የሚገመት መሆኑን አስረድተዋል።
በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተያዘ የነዳጅ ምርት 9,500 ሊትር ሲሆን ከ750,ሺህ ብር በላይ ሊያወጣ የሚችል መሆኑን ጭምር ተናግረዋል።
በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ የነዳጅ ምርት፣ በህገወጥ መንገድ ንግድ ሲካሄድ የተያዙ የተለያዩ ዕቃዎች በፋይናንስ መመሪያና አሰራር በኮሚቴ ንግድ ፈቃድ ላላቸው ነጋዴዎች እንዲሸጡና የተሸጠው ገንዘብ በፋይናንስ በአደራ አካውንት እንድቀመጥ ግብረኃይሉ ወስነዋል።
እንደ አርባምንጭ ከተማ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረኃይል ቀጣይ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ህብረተሰቡም ደግሞ ለዚህ ተባባሪ እንዲሆንና ከግብረኃይሉ ጎን እንድቆም አሳስበዋል።