የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ሀላፊና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም አስተባባሪ ቴክንክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ ሀለቃ ሀይለ ሚካኤል ጉላንታ እንዳሳወቁት አገሪቱ አሁን በገባችበት ሁኔታ በመደበኛ ስርዓት ሊተገበሩ በማይቻሉ ጉዳዮችን መሠረት አድርጎ በፌዴራል ደረጃ የወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎችን ለመተግበር የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ክልል መንግስት ከቀን 28/02/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ክልከላዎችን ማውጣቱን አሳውቀዋል ።
የክልሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላን ተከትሎ በአርባምንጭ ከተማ በየቀበሌው ለሚገኙ ነዋሪዎች አዋጁን አስመልክቶ የህዝብ ውይይት እየተደረገ መቆየቱን ተናግረው ለአገሪቱ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የህዝቦቿን ነፃነትና እኩልነት ለማስፈን የወጡ አዋጆችን በማስተግበሩ ረገድ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ አሳውቀዋል ።
በዚህም መሠረት
-. ማንኛውም ባለሁለት እግር ተሽከርካሪ ከቀኑ 12፡00 ሰዓት በኋላ እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ ነው፤
-. ማንኛውም የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ባለ ሶስት እግርን ጨምሮ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት በኋላ ማንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤
-. የምርት ዕንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል የጭነት መኪኖች በየኬላው ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገባቸው እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው ሆኖ ከረዳቱና ካሽከርካሪው ውጪ መጫን የተከለከለ ነው፤
- ከፀጥታ አካላት ውጪ ማንኛውም እግረኛ በክልሉ ውስጥ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤
- . ከጤና ተቋማት፣ ከነዳጅ ማደያዎች፤ ከፖሊስ ጣብያዎች ውጪ ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ ተቋማ ከምሽቱ 3፡00 በኋላ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፤
- . ማንኛውም ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪና አሽከርካሪ የመንግስትን ጨምሮ ከቀን 29/2/2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ቀን 3/3/2014 ዓ.ም ድረስ በአቅራብያቸው ባለው የፖሊስ ተቋም ቀርበው መመዝገብ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል ።